========================================
ይህ ሳምንት ከሰርከ ሆሳዕና እስከ ትንሣኤ ያሉትን ቀናት ያካትታል:: የጌታን መከራ እንግልት መሰቀል መሞት መቀበር የምናስብበት ነው:: ለእኛ ሲል የተቀበላቸውን 13ቱ ሕማማተ መስቀል በማሰብ በልቅሶ በስግደት በጸሎት ልናሳልፈው ይገባል:: በዚህ ሳምንት ሊሰሩ ያልተፈቀዱ በርካታ ናቸው:: በመስቀል መባረክ ማማተብ መሳቅ መሳሳም ከሴት ጋር መገናኘት ኑዛዜ መፈጸም ፈጽሞ የተከለከለ ሲሆን የ5500ው የጨለማ ዘመን መታሰቢያ በመሆኑ መንበሩ በጥቁር ልብስ ይሸፈናል ካሕናትም ጥቁር ይለብሳሉ:: በዚህ ሳምንት ለሞተ ጸሎተ ፍትሐት አይጸለይለትም ክርስትናም እንዲሁ አይፈጸምም:: እግዚአብሔር ይፍታህ አይባልም ሳምንቱ የሚታሰበው ሕማሙን ሞቱን በማሰብና በስግደት ነው:: የግዝት በዓላት እንኳ ይሰገድባቸዋል:: የዚህ ሳምንት ጾም የቻለ ሁለት ሁለት ቀን ያልቻለ እስከ ጀንበር ግባት ድረስ ነው:: ምግቡም ቆሎ ዳቦ የላመ የጣመ ያልሆነ ደረቁን በበርበሬ ነው መጠጡም ንጹህ ውኃ ነው:: ጠጅ ያንቆረቆረ ጮማ የቆረጠ እድል ፈንታው ጽዋእ ተርታው በጌታ ሞት ከተደሰቱት ከአይሁድ ጋር ነው:: ጸሎቱ ውዳሴማ ርያም አንቀጸ ብርሃን መልክአ ሕማማት መዝሙረ ዳዊት ነው:: የቅዱሳን መልክአ መልክእ አይጸለይም:: የጾሙ ሥርዓት ምን ይመስላል ካሉ፡
ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15
ቁጥር 578፡ በሊህ በስድስቱ ቀኖች (በሰሙነ ሕማማት) ከቂጣ ከጨው ከውኃ ብቻ በቀር አይብሉባቸው፡፡ በሊህ
ቀኖች ከወይን ከሥጋ ተለዩ የኀዘን ቀኖች ናቸውና የደስታ ቀኖች አይደሉም፡፡ዓርብንና ቅዳሜን ግን ሁለቱንም በአንድነት ጹሟቸው፡፡
የሚችል እስከ ሌሊቱ ዶሮ ጩኸት ጊዜ ድረስ ምንም ምን አይቅመስባቸው ሰውየውም ሁለቱን ቀኖች በአንድነት መጾም ባይቻለው ግን የቅዳሜን
ጾም ይጹም፡፡
ቁጥር 590፡ ካህን ሰሙነ ሕማማትን ቀንና ሌሊቱን ሳያስተካክል አስቀድሞ ቢያውል ይሻር፡፡ ከሕማማት ቀጥላ
ከምትሆን ከቅዳሜ ስዑር በቀር እሑድንና ቅዳሜን የጾመ ካህን ቢኖር ይሻር፡፡
ቁጥር፡ 593፡ ከካህናት ወገን ማንም ቢሆን በአርባ ጾም በዓርብና በረቡዕም ጾም ወይን መጠጣት አይገባውም
ወደ መዋት (ውሽባ ቤት) አይግባ፡፡ በዐቢይ ጾም ወራት ሰው ከሚስቱ ጋር አይተኛ፡፡
ቁጥር 597፡ ሴቶችም ጌጣቸውን ይተው፡፡ ሁሉም ለእያንዳንዱ በአርባ ጾምና በሰሙነ ሕማማት መጠበቅ ይገባዋል
ድኅነታችንና የኃጢአታችን ሥርየት በእነርሱ ነውና፡፡ ይኸውም ሥራ አንዱስ እንኳ በአርባ ጾም ወራት በምንጣፍ ፈጽሞ እንዳይገናኝ
ከጋብቻ ሕግ የወጣ ነው፡፡ ክብርት በምትሆን በሕማማት ወራት ይህችን ኃጢአት የሚሠራት ሰው ወዮለት፡፡ በአርባ ጾም በተድላ በደስታ
ፈቃዳችንን ካደረግን ትንሣኤውን ባየን ጊዜ ተድላ ደስታችን ወዴት አለ?
ቁጥር 599፡ በተባሕትዎ በትሕትና አርባ ቀን ጾምን ይጹሙ፡፡ ከጥሉላት መከልከል ይገባል፡፡ አያግቡም፡፡
ቁጥር 600፡ በሰሙነ ሕማማት ክርስትና ማንሣት ክህነት መስጠት ለሞቱ ሰዎች መጸለይ አይገባም፡፡ በእነዚህም
ቀኖች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ፈጽሞ ማገልገል ይገባል እንጅ፡፡ በሰሙነ ሕማማት ስለሚሞቱት ሰዎች የሙታን ግንዘትና የሐዋርያት ሥራ
ወንጌላት የሙታን ፍትሐት በሆሣዕና በዓል ቀን ይነበብ እንጅ፡፡
ቁጥር 601፡ በጸሎተ ሐሙስ ጸሎተ ተአምኆ እግዚአ ሕያዋን የቡራኬ ጸሎት አይባልም (አይጸለይም)፡፡ ቅዳሜ
ግን እግዚአ ሕያዋን ይባላል ፍትሐት ይፈታል፡፡ ከመሳለም በቀር ጸሎተ ዕጣንም ይጸለያል፡፡ በዕለተ እሑድ ግንዘት ማድረግ በፋሲካ
ቀንም ማልቀስ አይገባም፡፡ ዳግመኛም በውስጧ በአርባ ጾም ከተድላ ከደስታ ወገን ምንም ማድረግ አይገባም፡፡ መጋባት ክህነት መስጠት
ክርስትና ማንሣት ከሹመትም ወገን ስለሚሞቱት ከመጸለይ በቀር ምንም ማድረግ አይገባም፡፡ ይሞታል ተብሎ ለሚያስፈራው ግን ጥምቀተ
ክርስትና ይደረግለታል፡፡
የተከለከሉ ነገሮች
ምን ምን ናቸው ካሉ፡
- 1. እጅ ተጨባብጦ ሰላምታ መባባል መሳሳም
- 2. ሩካቤ ሥጋ ማድረግ
- 3. መስቀል ማሳለም እና መሳለም
- 4. ክርስትና ማስነሣት
- 5. ለሙታን ፍትሐት ማድረግ
- 6. ክህነት መስጠት
- 7. የላመ የጣመ ምግብ መመገብ
- 8. መሳቅ መጫዎት መጨፈር
- 9. አብዝቶ ጠግቦ መመገብ
- 10. መስከር ወዘተ ናቸው፡፡
የሳምንቱ ዕለታት በሙሉ የሚታሰቡበት ሥራ ተሰርቶባዋቸል እንደሚከተለው እንመልከት፡፡
- v ሰኞ:- ጌታ ቅጠል ብቻ ሆና ያገኛትን ዕጸ በለስ የረገመበት ቀን ነው:: ማር11÷ 20-22
- v ማክሰኞ:- የትምህርት ቀን ነው:: ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተ መቅደስ ካሕናትና አለቆች ለጠየቁት ጥያቄ ረዥም ትምህርትን ሰጥቷል:: ማቴ21÷ 23-27
- v ረቡዕ:- ምክረ አይሁድና የሽቱ ቀን ይባላል:: አይሁድ ክርስቶስ ተሰቅሎ እንዲሞት የወሰኑበት ዕለት ነው:: በዚህም ዕለት ጌታ በስምዖን ዘለመጽ ቤት ሳለ ማርያም ባለሽቱዋ ሽቱ እያርከፈከፈች በእንባዋ እግሩን እያራሰች በጠጉሯ የጠረገችበትና ኃጢአቷን ይቅር ያለበት ዕለት ነው:: ይሁዳ ሰላሳ ብር የተመዘነለትም ዕለት ረቡዕ ነው:: ማቴ26÷1-16
- v ኀሙስ:_ ጸሎተ ኀሙስ ማር14÷22፣ ዮሐ17፣ ማቴ26÷36 ትዕዛዘ ኀሙስ ዮሐ13÷11፣ ማቴ26÷36 የነጻነት ኀሙስ ዮሐ15÷15 ሕጽበተ እግር ዮሐ13÷11ጌታ የደቀመዛሙርቱን እግር ያጠበበት የሐዲስ ኪዳንን የቁርባን ሥርዓት የሠራበት ያሳየበት ያስተማረበት ዕለት ነው፡፡
- v አርብ:- ረቡዕ የመከሩትን የስቅላት ውሳኔ የፈጸሙበት ክርስቶስ የተሰቀለበት ዕለት ነው:: ሞትን ሊሽር ሞተ ሞትን ሊያጠፋልን ሞተ የጥል ግድግዳችንን ሊያፈርስ የማይሞተው ሞተ::
- v ቅዳሜ:- ቅዳም ስዑር በጾም የተሻረች ቅዳሜ የጌታን ትንሣኤ እስኪያዩ ድረስ ስለጾሙት እኛም አክፍሎት ብለን ቅዳሜን ስለምንጾማት የተሻረች ቅዳሜ እንድትባል አድርጓታል:: መሻሯ በጾም እንጅ በሥራ አይደለም፡፡
- v እሁድ:- ትንሣኤ ይባላል፡፡ መቃብርን ድል ነስቶ ከሌሊቱ 6 ሠዓት በኃይሉ ተነሣ:: ሞታችንን ሊያጠፋ የሞተልን አምላክ በክብር ተነሣ፡፡ እልልልልልልልልልል... የሞት ሥልጣን ተሻረ:: እንደ በግ በግፍ የተጎተተው ወልደ ማርያም ከቁስላችን ሊፈውሰን ስለእኛ ቆሰለ በዕለተ አርብ በመልዕልተ መስቀል ዋለ:: አርብ በ 9 ሰዓት የድኅነት ሥራየ እና በነቢያት የተነገረው ሁሉ ተፈጸመ አለ:: ራሱንም ወደቀኝ ዘንበል አድርጎ ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው በፈቃዱ ለየ:: በ 11ሰዓት የአርማትያሱ ዮሴፍና በሌሊት ከጌታ ዘንድ እደሄደ ይማር የነበረው ኒቆዲሞስ ሥጋውን አውርደው “ቅዱስ እግዚአብሔር” እያሉ ገንዘው በአዲስ መቃብር ቀበሩት:: በአካለ ሥጋ ወደ መቃብር ሲወርድ በአካለ ነፍስ ወደ ሲዖል ወርዶ የሲዖል ነፍሳትን በሙሉ በርብሮ አወጣቸው ሲዖልም ባዶዋን ቀረች:: እርሱ ግን እንደተናገረው በኃይል በክብር በስልጣን ተነሣ:: “ወተንሥአ እግዚአብሔር ከመ ዘንቃህ እምንዋም፡፡ ወከመ ኃያል ወኅዳገ ወይን፡፡ ወቀተለ ጸሮ በድኅሬሁ” እንዳለ ክቡር ዳዊት፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ በከርሠ መቃብር 3 ቀንና 3 ሌሊት አደረ፡፡ ይኸውም ነቢዩ ዮናስ በዓሣ አንበሪ ሆድ እንዳደረው (ዮና 2÷1-2) ራሱም መድኅን ዓለም ይህን ቤተ መቅደስ
አፍርሱት በ3 ኛው ቀን አነሣዋለሁ ብሏል፡፡ (ዮሐ2÷19-22 ) የተሰቀለ አርብ 6 ሰዓት ነፍሱን ከሥጋው የለየው አርብ 9 ሰዓት ወደ መቃብር የወረደ አርብ 11 ሰዓት የተነሣ ቅዳሜ ለእሁድ ሌሊት 6 ሰዓት ነው፡፡ ይህ 3 ቀንና 3 ሌሊት እንዴት ተባለ? ቢሉ የመጀመሪያው ብርሃኑን “ቀን” ጨለማውን “ሌሊት” በማለት የሚቆጠረው አቆጣጠር ነው፡፡ ይኸውም ቀኖቹ:-
- v አርብ ከነግህ እስከ 6 ሰዓት ብርሃን ነበር
- v ከ9 ሰዓት እስከ ሰርክ ብርሃን ነበር
- v ቅዳሜ ቀን
ሌሊቶቹ:-
- v አርብ ከ 6 ሰዓት እስከ 9 ሰዓት ጨለማ
- v አርብ ለቅዳሜ ሌሊት
- v ቅዳሜ ለእሁድ ሌሊት
ሌላው በእዕብራውያን የቀን አቆጣጠር መሠረት ዓርብ ሌሊቱን እሁድ ቀኑን
ይስቡና ይቆጠራል፡፡ ይኸውም:- ሌሊቶቹ
- v ሐሙስ ለአርብ
- v አርብ ለቅዳሜ
- v ቅዳሜ ለእሁድ
ቀኖቹ ደግሞ
- v አርብ ቀኑን
- v ቅዳሜ ቀኑን
============================================================================
በመጨረሻ ይህንን ገጽ ላይክ ያድርጉ፡፡
facebook.com/tomarthetewahido
============================================================================
ሐምሌ ፳፩/፳፻፱ ዓ.ም
#share ᎘᎘
#like ᎘᎘
#comment ᎘᎘
#ጦማር_ዘተዋሕዶ
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ