ዛሬ መስከረም 18/2010 ዓ.ም ነው፡፡
ይህ መረጃ በነሐሴ ወር የተደረገውን ስብሰባ የሚያስተነትን ነው፡፡ ይህን
መረጃአቀርብላችኋለሁ ብየ ቃል ከገባሁላችሁ በኋላ እስከዛሬ ያዘገየሁበት የራሴ ምክንያት ስላለኝ ነው፡፡
1ኛ. መረጃውን እውነተኛ ለማድረግ ተሰብሳቢዎችን ማነጋገር ስለነበረብኝ፡፡
2ኛ. በወር ውስጥ የመጣውን ለውጥ በድጋሜ ተሰብስበው እንደሚገመግሙ ስለተነገረኝ
የተፈጸመ እና ያልተፈጸመውን በአግባቡ እንዲያነሡት መረጃውን ለመስጠት ነው፡፡
ቀኑ ነሐሴ /2009 ዓ.ም ነው፡፡ ሃይማኖታዊ እና አስተዳደራዊ በደሎች
እየተፈጸሙባቸው ያሉ የምሥራቅ ጎጃም ምእመናን ጉዳያቸውን በግልጽ ከመንግሥት አካላት ጋር ለመነጋገር የምእመናን ተወካዮች በአንድ
በኩል የችግር ፈጣሪው ቤተክህነት ተወካዮች በሌላ በኩል ሆነው የመንግሥት አካላትን እና ሌሎች ታዛቢዎችን በመካከላቸው በማድረግ
ውይይታቸውን ለማድረግ የስብሰባ ቦታቸው ወደሆነው የምሥራቅ ጎጃም ዞን አብቁተ ሕንጻ አዳራሽ ተሰበሰቡ፡፡ የስብሰባው ዋና ዓላማ፡- በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በአቡነ
ማርቆስ፣ በሊቃነ ካህናትና ፣ በአጥቢያ አስተዳዳሪዎችና በምእመናን መካከል የተፈጠረውን ሃይማታዊ እና አስተዳደራዊ አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት ታስቦ የተጠራ ስብሰባ ነበር፡፡
ምንም እንኳ አለመግባባቱ የተፈጠረበት ዋነኛው ምክንያት ሃይማኖታዊ ጉዳይ ቢሆንም በዚህ ስብሰባ ግን ለውይይት የቀረበው ጉዳይ
አስተዳደራዊ ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ ሃይማኖታዊ የሆነውን ጉዳይ ግን ቤተ-ክርስቲያኗ በራሷ መዋቅር(ሲኖዶስና ጠቅላይ ቤተ-ክህነት) ልታየውና
ልትዳኘው የምትችለው ጉዳይ በመሆኑ የዞኑ መንግሥት በሁለቱም ወገን
አስተዳደራዊ የሚባሉ ችግሮችን አዳምጦ የጋራ መፍትሔ ለማስቀመጥ ታሳቢ ተደርጎ የተካሄደ ስብሰባ ነው፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች እንዲሆኑ የተጠሩ
አቡነ ማርቆስ የምሥራቅ ጎጃም ሐገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ጥሪ የተደረገላቸው እና በስብሰባው ሊገኙ ቃል የገቡ ቢሆንም እርሳቸው
ግን ስብሰባው ሊጀመር ሲል በአስራ አንደኛው ሰዓት እንደማይመቻቸው
መግለጻቸውን የዞኑ አስተዳዳሪ ለታዳሚው የተናገሩ ሲሆን ሁለት አማራጮችን ለታዳሚውም አቅርበው ነበር ፡፡ የመጀመሪያው አቡነ ማርቆስ በሚገኙበት ቀን በአስቸኳይ ሌላ ስብሰባ መጥራት ሲሆን ሁለተኛው
አማራጭ ደግሞ ተወካዮቻቸው ስላሉ ስብሰባውን ማስቀጠል የሚል ነበር፡፡ በዚህም መሠረት የተሻለው አማራጭ ሁለተኛው አማራጭ ስለነበር
ስብሰባው እንዲቀጥል በመስማማት ስብሰባው ከጠዋቱ 2፡30 እስከ ምሽቱ 2፡00 ድረስ ተኳሂዷል፡
የመንግስት አካላት (የዞን ከፍተኛ አመራሮችና የደ/ማርቆስ ከተማ ከንቲባ፣ አስተዳደርና ጸጥታና የፖሊስ ኃይሎች)
የደ/ማርቆስ ዩኒቨርስቲ ፕሬዘዳንት ዶ.ር ንጉሤ ምትኩ፣ የደ/ማርቆስ ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች ፕሬዘዳንትና የዩኒቨርስቲው ጸጥታ
ዘርፍ
የሀገረ ስብከት፣ የወረዳ ቤተ-ክህነት ሰራተኞች እና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች በአጠቃላይ በቤተ-ክህነቱ በኩል 25-30 የሚደርሱ ተወካዮች ጥሪ ተደርጎላቸዋል፡፡
የምእመናን ተወካዮች (ከሀገረ ስብከት ሕንጻ አሰሪ ኮሚቴዎች፤ ከባህረ
ጥምቀት አሰሪ ኮሚቴዎች) የማኅበረ ቅዱሳን አመራሮች፣ የሰ/ት/ቤት ተወካዮች ከሁሉም አድባራት፣ ከምእመናን በኩል በቁጥር 30 አባላት ጥሪ ተደርጎላቸው ተገኝተዋል፡፡
የስብሰባ አጠቃላይ ሁኔታ
o ሞባይል ይዞ መግባት በጥብቅ የተከለከለ ሲሆን አዳራሹ መግቢያ በር ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር የተደረገበት ፍተሻ ነበር፡፡
o መድረኩን የመሩት (የዞኑ አስተዳዳሪ ፣ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አማካሪና የደ/ማርቆስ ከተማ ከንቲባ) ነበሩ፡፡
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ የስብሰባውን አካሄድ የሚከተሉትን
አምስት ነጥቦችን በማስቀመጥ አብራርተዋል፡፡
1.
የቤተክርስቲያን አስተዳደራዊ ጉዳዮች በሙሉ እንዲነሡ
2.
ዋና ዋና ጉዳዮችን
-
የግል ጉዳዮች ባይቀርቡ ምክንያቱም አቤቱታ ስለሚሆን ስለዚህ የጋራ ጉዳዮች በሆኑ
ላይ ማተኮር እንደሚገባ፡፡
-
የሚነሱ ጉዳዮች ሀገረ ስብከቱን የሚመለከቱ በዞናችን ያሉ ጉዳዮችን በሚዳስስ መልኩ
እንዲቀርብ፡፡
3.
ለሁሉም ሰው እድል መስጠት አስቸጋሪ ስለሆነ ከሁሉም ተወካይ የስብሰባው ተሳታፊ
እንዲሆን ጥሪ ስላስተላለፍን በተወካይ በኩል እንዲቀርብ ቢደረግ፡፡
4.
የተሳታፊውን ንግግር በተመለከተ
-
ሃይማኖታዊ ስነ-ምግባሩን የተላበሰ እንዲሆን
-
ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለው እንዲሆን
-
ሰዎች ላይ ሳይሆን ጉዳዩ ላይ ብቻ ብናተኩር፡፡
5.
የሰዓት ገደብ ቢኖረውና አንድ ሰው ሀሳቡን በተሰጠው ደቂቃ ውስጥ በፍጥነት እንዲያጠቃልል
ቢደረግ፡፡
የሚለውን ንግግር የዞኑ አስተዳዳሪ ካደረጉ በኋላ የስብሰባው አካሄድ የነበረው በመጀመሪያ ምእመናን በቤተ-ክህነቱ በኩል የሚደርሱ አስተዳደራዊ በደሎችን እንዲዘረዝሩና
ቀጥለው ደግሞ ቤተ-ክህነቱ ከምእመናን ለተነሡ ጥያቄዎች መልስ እንዲሰጡ
እና በተጨማሪም በምእመናንም በኩል ይፈጠራሉ የሚሏቸውን ችግሮች እንዲያነሱ
የሚል ነበር፡፡ ይህ በዚህ መልኩ ከተፈጸመ በኋላ በመጨረሻ መፍትሔ
እንዲያስቀምጡ የሚለውን አካሄድ አስተዳዳሪው ገለጻ ካደረጉ በኋላ ውይይቱን ለተሳታፊው አስተላልፈውታል፡፡
በዚህም መሠረት በመጀመሪያ እድሉ የተሰጠው ለሰ/ት/ቤቶች ነበር ከዚያም ቀጥሎ ለማኅበረ ቅዱሳን ከዚያም ለሌሎች ምእመናን
ተወካዮች ቀጥለዋል፡፡
አጠቃላይ በምእመናኑ በኩል የቀረቡ አስተዳደራዊ በደሎች ጠቅለል ሲሉ የሚከተሉት ናቸው፡፡
በምእመናን በኩል የተነሱ አስተዳዳራዊ በደሎች
1.
ሰ/ት/ቤቶች ተዘግተዋል ፡፡ ወጣቱ ወደ እናት ቤተ-ክርስቲያናቸው
እንዳይመጡ እያደረጉን ነው፡፡
2.
ከወረዳ የመጣ የሰ/ት/ቤት አባል መሆን አይችልም በሚል አስተዳደራዊ
እና ሃይማኖታዊ ጥያቄ የሚጠይቁ የሰ/ት/ቤት አመራሮች ከሰ/ት/ቤት አባልነት እየተባረሩ ነው፡፡ በተለይ የመልእልተ አድባራት ቅዱስ
ማርቆስ አስተዳዳሪ ቆሞስ አባ ወልደ ትንሳኤ ባንቲገኝ በዚህ የታወቁ ናቸው፡፡ ለዚህም በቂ የሆነ ማስረጃ አለ ተብሏል፡፡
3.
በእመቤታችን ጾምና በጾመ ኢየሱስ የሚካሄደውን የማኅበር ጸሎተ
ምሕላና ስግደት እንዲቋረጥ አድርገዋል ፡፡
4.
የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ቤተ-ክርስቲያን ሄደው እንዳይማሩ የማድረግ
ስራ እየተሰራ ነው፡፡ በትውልድ አካባቢ በመከፋፈል በተማሪዎች መካካል አለመግባባት እየፈጠሩብን ይገኛል፡፡
5.
አብዛኛዎች አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ሰበካ ጉባኤ የላቸውም፡፡
የምእመናን ተወካዮችና የሰ/ት/ቤቶች ተወካዮች ከሰበካ ጉባኤ እንዲወጡ ተደርገዋል፡፡ በዚህም የዘመዳ ዘመድ ስብስብ ብቻ ያለበት
ሰበካ ጉባኤ በመሆኑ ቤተ-ክርስቲያናችን እየተመዘበረች ትገኛለች፡፡
6.
ቅርሶቻችን እየተዘረፉብን ነው ፡፡ አባቶቻችን ያወረሱን ቅርሶች
እየተዘረፉ በመሆኑ ለአቡነ ማርቆስ ጥያቄ ብናቀርብም “እኔ ቅርስ ልጠብቅ የመጣሁ አይደለሁም” የሚል አሳዛኝ መልስ ሰጥተውናል ተብሏል፡፡
7.
የገንዘብ ዝርፊያ ከሚገባው በላይ እየተካሄደብን ነው ፡፡ ለምሳሌ
በጣም ብዙ ብር በቀን ገቢ የሚደረግበት የገዳመ አስቄጥስ አቡነ ተ/ሃይማኖት ገዳም የሒሳብ አካውንት ከጥር 17/2009 ዓ.ም ጀምሮ
በአቡነ ማርቆስ፣ በአባ እንባቆም የሀገረ ስብከቱ ስራ አስኪያጅና አባ ብርሃነ መስቀል የገዳሙ አስተዳዳሪ ስም እንዲቀሳቀስ መደረጉና
አስገራሚው ጉዳይ ደግሞ ከሦስቱ ሁለቱ ፈራሚዎች ከተገኙ እንዲንቀሳቀስ በሚል ነው አካውንቱ የተከፈተ ፡፡ ስለዚህ የገዳማችን ብር
ለዝርፊያ ምቹ ሆኗልና በቀደመው አሰራር እንዲቀጥልልን የሚል ጥያቄ ከገዳሙ ተወካዮች ቀርቧል፡፡
8.
ቤተ-ክህነቱ የአንድ ቤተሰብ ስብስብ በመሆኑ አቤቱታችንን ለማን
እናቅርብ ፡፡ ይህን እውነታ ለማሳያ የአቡኑን ትንሽ ወንድም አራት ልጆችና የእህታቸውን (የወ/ሮ በላይነሽ ተፈራን) ሦስት ልጆች
በስም ዝርዝር ለማሳያነት ጠቅሰዋል ፡፡ የሚገርመው ከእነዚህ መካከል አንደኛው የሀገረ ስብከቱ ልማት መምሪያ ም/ኃላፊ ብዙአየሁ ገደፋው በሁለቱም በኩል (በዓለማዊም
በመንፈሳዊም) ምንም ያልተማረ መሆኑና እንደተቀጠረ ሰሞን በዱካ የሚፈርም እንደነበረ ተነሥቷል፡፡
9.
የደመወዝ ሁኔታና መደብ አለመጣጣም፡፡ ለምሳሌ ከ30ና 40
ዓመት በላይ ያገለገሉ መምህራን ግን የሥጋ ዝምድና የሌላቸው ደመወዛቸው ከ2000 ብር በታች ሲሆን አንድ መዝገብ ቤት የሥጋ ዝምድና
ያላት በዚያው ላይ አንድ ዓመት እንኳ አገልግሎት ግዜ ያልሞላት ሴት 3500 ብር መክፈል ሌላኛ የአቡነ ማርቆስ አስተዳደር ግፎች
ናቸው ተብሎ ተነሥቷል፡፡
10. ለአጥቢያ ሰበካ ጉባኤ በቋሚ ቅጥር የመቅጠር ሁኔታ እጅግ አስቸጋሪና ገንዘብ ለመመዝበር ታስቦ ከታቀደ እቅድ ውስጥ አንዱ
ነው፡፡ ቅጥሩ የሚፈጸመው የዝምድና ሀረጉን ብቻ ጠብቆ ነው፡፡ የሚያስቀምጧቸው ሰዎችስ እውን ውጤት የሚያሳዩ ናቸው ወይ ????
ምሳሌ እናንሳ የቅዱስ ሚካኤል ሰበካ ጉባኤ ጸሐፊ (ዲ/ን) በረከትሞላ ይህንን ያሟላል ወይ ???? በስነ-ምግባር ከአጥቢያው ቢነሳ ቅጣቱ የሚያሳዝን
ነው ባለው ደመወዝ ላይ 870.00 ብር ጨምሮ ወረዳ ቤተ-ክህነት ላይ ማስቀመጥ ምን የሚሉት እብደትና ንቀት ነው ተብሏል፡፡ በነገራችን
ላይ ይኼ ልጅ ከሴት ጋር የማይገባ ሥራ ሠርተሃል ተብሎ ከዋሻው ቅዱስ ሚካኤል የተባረረ የአቡነ ማርቆስ ዘመድ ነው፡፡ ከዋሻው ቅዱስ
ሚካኤል ከቀዳሽነቱ ሲባረር ሀገረ ስብከት ላይ ብር ጨምረው አቡነ ማርቆስ ቀጥረውታል ለምን ዘመድ ስለሆነ ሌላ ምን አለው ብላችሁ
ነው፡፡
11.
ሀገረ ስብከቱ ለሚያስገነባው ሕንጻ ማስጨረሻ በሚል ከፍተኛ
የሆነ ገንዘብ ለመበደር ደፋ ቀና እያሉ ነው፡፡ ይህን ገንዘብ ይዞ ለመሄድ ነው ስለዚህ ይሔ ጉዳይ እንዲቆም አንደኛ በአቡነ ዘካርያስ ጊዜ የጠፋው ብር ተመላሽ ስለሆነ እርሱ ብር የት ደረሰናነው
ብድር መጠየቁ ፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የተመለሰው ብር የእኛ ብር ስለሆነ ለምን ይፋ አይደረግም በዚያውም ላይ ከጠፋው ብር ውስጥ
500,000.00 ብሩ የሞጣ ወረዳ ቤተ-ክህነት 140,000.00 ብሩ ደግሞ የአስቄጥስ አቡነ ተ/ሃይማኖት ገዳም
ብር ስለሆነ ለምን ለባለቤቶቹ ድርሻቸው አይሰጥም የሚልም አብሮ የተነሳ
ጉዳይ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ይህ የሀገረ ስብከቱ ህንጻ አሁን መስከረም 27 እና 28 ይመረቃል ተብሏል፡፡ በዚህ ህንጻ ስምም
አቡነ ማርቆስ ገንዘብ ሊበደሩበት ሲሉ ከባንክ ቤቶች ጋር በተሠራ ከፍተኛ ጥረት ከሽፎባቸዋል፡፡
12. የቅባት ምንፍቅና መጻሕፍት ሲጻፉ እና የምእመናን ፊርማ ተሰባስቦ ሲቀርብላቸው ምንም ዓይነት መልስ አለመስጠት የሚለው
ጉዳይም ተነሥቷል፡፡ ከብዙዎቹ በጥቂቱ የተነሡት እነዚህ ነጥቦች ሲሆኑ በዚህ ጉዳይ ላይ እንዲናገሩ እድሉ ለቤተ-ክህነቱ
መዋቅር ተሰጥቷል ፡፡
ዋና አስተዳዳሪው እድሉን ከመስጠቱ በፊት ሲናገሩ ከዚህ በታች የተዘረዘሩ ነጥቦች መነሻ በማድረግ እንዲሆን ማሳሰቢያ
ሰጥተዋል፡፡
·
ችግር የፈጠሩባችሁ ምእመናን ካሉ ችግሩን እንድትገልጡ
·
መልስ(በቅሬታ የቀረበባችሁ) አካላት
·
ቀድሞ የነበሩ አሰራሮች ለምን ተዘጉ? የሚሉ ጉዳዮችን በንግግራቸው እንዲያነሱ አሳስበዋል፡፡
ከዚያም ቅድሚያ ለአጥቢያ አስተዳዳሪዎች ቀጥሎ ለወረዳ ቤተ-ክህነትና በመጨረሻ
ለሀገረ ስብከት ተወካዮች እድሉን የሠጡ ሲሆን የመጀመሪያውን እድል የተሰጠው ለመጀመሪያው ዋና የችግሩ ፀብ አጫሪ ለሆኑት ለእድማጣው
አስተዳደሪ መልአከ ገነት ሙሉ አያሌው ነው፡፡ እነኝህ አስተዳዳሪ በዋናነት የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲን ዋና ግቢ ጉባዔ ለማፈራረስ
ከአቡነ ማርቆስ ተልእኮ ተሰጥቷቸው የተመደቡ ናቸው፡፡ በአቡነ ማርቆስ የማእረግ አጠራር ደግሞ አንተ ጀግና ነህ ማኅበረ ቅዱሳንን
ታግለሃልና ከዛሬ ጀምሮ “በላይ ዘለቀ” ብየሃለው የተባሉም ሰው ናቸው፡፡ በላይ ዘለቀ ለሀገሩ የሞተ የኢትዮጵያ ጀግና ሲሆን የአቡነ
ማርቆሱ በላይ ዘለቀ(መልአከ ገነት ሙሉ አያሌው ) ግን ለሆዱ የሚሞተው ገንዘብ ያሣወረው ሰነፉ በላይ ነው፡፡ ስለዚህ ሁለቱም ስሞቻቸው
በላይ ዘለቀ መባላቸውም ሆነ መልአከ ገነት መባላቸው ቢሆኑ ለእርሳቸው የሚመጥኑ አይደሉም፡፡
በቤተ-ክህነቱ በኩል የተነሱ ችግሮች
1.
የእንድማጣው አስተዳዳሪ ዓይናቸውን በአቡነ ማርቆስ ጨው አጥበው እውነቱን ሀሰት
ሀሰቱን እውነት በማለት ወተቱን አጥቁረው ማሩን አምርረው እንደተናገሩት ግዙፍ የሆነ ካቴድራል እየገነባን ነው ፡፡ ነገር ግን ግቢ
ጉባኤ ድጋፍ እያደረገልን አይደለም ብለዋል፡፡ የዚህንም እውነታ ለማረጋገጥ ከግቢ ጉባዔው መረጃ ማሰባሰብ ነበረብኝ ይህንንም በፎቶም
በቪዲዮም በሰነድም የተደገፈ ማስረጃ በማፈላለግ ለማረጋገጥ ችያለሁ፡፡ በዚህም መሠረት ግቢ ጉባዔው፡-
-
በ2005 ዓ.ም የመሠረት ድንጋይ ሲጣል 25000 ብር መስጠቱን አረጋግጫለሁ፡፡
-
በ2006ና 2007 ዓ.ም መቶ መቶ በድምሩ 200 ኩንታል ሲሚንቶ ገዝተው ገቢ አድርገዋል፡፡
-
በ2008 ዓ.ም 76000.00 ብር ገቢ አድርገዋል ፡፡ ይህን ብር ግቢ ጉባዔው
የሰጠው በዲፓርትመንትና በባች ተከፋፍለው የራሳቸውን የገቢ ማስገኛ
ዘዴ በመጠቀም መሆኑን ለመረዳት ችያለሁ፡፡ የግቢ ጉባዔው እቅድ የነበረው ሙሉ ብሉኬት መቻል የነበረ ሲሆን የደብሩ ጸሐፊና አስተዳዳሪ
ብሉኬት በመግዛታችን ለእነርሱ የሚያገኙት ጥቅም ባለመኖሩ ብሉኬት አንፈልግም ብሩ በጥሬ ብቻ ይሠጠን በሚል ባቀረቡት ሀሳብ ነበር
ገንዘቡ የተሠጠው ፡፡ አገልግሎት ተሸንፎ ማሸነፍ ነው በሚል እንጅ ብሩን የት እንደሚያደርሱት አስቀድሞ የሚታወቅ ሀቅ ነው ይላሉ
አመራሮቹ፡፡
-
በ2009 ዓ.ም ደግሞ የ40ሺህ ብር ብሉኬት ገዝተው ብሎኬቱ ከሚመረትበት እስከ
ቤተክርስቲያኑ ድረስ በራሳቸው በጀርባቸው በትክሻቸው እየተሸከሙ ማድረሳቸውን መላው የደብረ ማርቆስ ህዝብ ምስክር ነው ይህንን እኔም
ዕድሉን አግኝቸ ተመልከቻቸዋለሁ ሲሰሩት በነበረውም ሥራ ከልቤ ቀንቸባቸዋለሁ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የክረምት ግቢ ጉባኤ ሌላ ተጨማሪ
ገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸው ተረጋግጧል፡፡
-
ሌላው ከዲዛይን እስከ ክትትል ያለውን የማኅበሩ ሙያና አቅም ማጎልበቻ ክፍል በነጻ
የሰራው መሆኑን ተረድቻለሁ፡፡
-
የጉልበት ሰራተኛ የሚወጣ ወጭ የለም የግቢ አባላት ሴት ወንድ ሳይሉ ነው የሚሰሩት
፡፡ የስላብ ሙሊት ሳይቀር የሞሉት የግቢ ጉባኤው ተማሪዎች ናቸው፡፡
2.
ሌላው የተነሣው ነጥብ የግቢ ጉባኤው አዳራሽ ያለበት ቦታ
የቤተ-ክርስቲያኗ ካርታ ውስጥ ስለሚገኝ የአጥቢያው ነው ብለዋል፡፡ ይህ እንደ ሀሳብ መነሣቱ የአስተዳዳሪውን ማንነት ፍንትው አድርጎ
ያሳያል ፡፡ ይህ አዳራሽ እኮ ዩኒቨርሲቲው ሥራ ከጀመረበት ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ በተሰበሰበ የግቢ ጉባዔ ተማሪዎች የተገነባ ነው፡፡
እነዚያ ይህንን ህንጻ ያሠሩት የግቢው አባላት ዛሬ የት ናቸው፡፡ ይህ ህንጻ እኮ ንብረትነቱ ለቤተክርስቲያኒቱ ነው የግለሰብ አዳራሽ
አይደለም፡፡ ደግሞስ ቢሆን አዳራሹን ግቢ ጉባዔው ሠራው ተብሎ ይነገራል እንጅ አዳራሹ የግቢ ጉባዔው ነው የሚል ሰው አለ እንዴ፡፡
ያማ ቢሆን ኖሮ ይህን ያህል ፈተና ስታደርሱበት ግቢ ጉባዔው ሃብቴ ንብረቴ ነው ብሎ በሸጠው ነበር ግን አይደለም የእናታችን ቤተክርስቲን
ሀብት ነውና አይደረግም፡፡ አስተዳዳሪው አለመረዳታቸው ነው እንጅ አይደለም አዳራሹ ልጆች ራሳቸው እኮ የቤተ-ክርስቲያን ናቸው፡፡ ታዲያ እነርሱ የቤተ-ክርስቲያኑ
ከሆኑ ቤተክርስቲያኑስ የእነርሱ አይደለም ወይ ብሎ ለሚጠይቅ ሰው
መልስ እንኳ መስጠት አይችሉም፡፡ በእርግጥ ቄስ ሙሉ አያሌው በተፈጥሮ
እንዲያስቡበት የተሰጣቸው አእምሮ ለሆዳቸው አሳልፈው የሰጡ ሰው ስለሆኑ ምንም ይጠየቅ ምንም የሚመልሰው የገንዘብ መልስ/ጥያቄ ብቻ
ነው ፡፡
3.
ዳግም ጥምቀት አለ ብለው አንስተዋል፡፡ የማይደገመው ምሥጢር በእውነት ተደግሟልን
ብለን ስንመለከት ግን ከእውነት የራቀ ነው፡፡ እየተጠመቁ ያሉት የቅባት እምነት ውስጥ የነበሩ ሰዎች እንጅ የተዋሕዶ ልጆች ስላልሆኑ
ይህ ተቀባይነት የለውም፡፡
4.
የሽንት ቤት ቁልፍ ተዘግቶብናል ብለው አንሥተዋል፡፡ አንድ የበግ እረኛ ሽንት ቤት
ተቆልፎብኛል የሚል አስቂኝ ነገር ሲያቀርብ መስማት ያሳዝናል እነርሱ ቤተክርስቲያንን መዝጋታቸው ምንም ሳይመስላቸው ስለሽንት ቤት
መዘጋት ማውራት ያሳፍራል፡፡
5.
በአማርኛ ውዳሴ ማርያም እናድርስ ይሉናል የሚልም አንሥተዋል፡፡ ይህ አባባል ከእኛ
ከካህናት ውጭ ግእዝ የሚችል የተማረ ሰው የለም ለማለት የታሰበ ንግግር ነው፡፡ የሚገርመው ነገር አንደኛ እውቀት የእምነት መገለጫ
አለመሆኑ ነው፡፡ ለዚህም የእውቀት ሰዎች የሚባሉትን ግኖስጢሳውያንን ልብ ማለት ይገባል፡፡ ሌላው እግዚአብሔር በአማርኛ ሲነገር
አይሰማም ወይ የሚለውን ጥያቄ መመለስ አለመቻላቸው ነው፡፡ ሆኖም ግን ይህ ብዙ ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ አይደለም፡፡
6.
ኪዳን አያደርሱም የምሕላ ጸሎቱን ከጨረሱ ወደ ግቢ ነው የሚሄዱት
የሚሉ አሳፋሪ ነገሮች የእንድማጣው በላይ ዘለቀ አቅርበውታል፡፡በነገራችን ላይ ቄስ ሙሉ ደብረ ማርቆስ ከመጡ ሁለት ዓመት የሞላቸው
ቢሆንም ኪዳን ላይ ተገኝተው አያውቅም ፡፡ ግቢ ጉባኤያቱ ጸሎት አድርገው ሲመለሱ እርሳቸው ወደ ቤተ-ክርስቲያን ሲሄዱ መንገድ ላይ
ስለሚገናኙ ነው የእርሳቸው የኪዳን ተራ(ሰዓት) ገና ስለሆነ ነው ፡፡ ኪዳን ለእርሳቸው ብር አምጡ ማለትና ስብሰባ መሰብሰብ ብቻ
ነውና ነው ፡፡ ልብበሉ እኒህ ሰው ኪዳኑን የሚችሉት አይመስልም ምክንያቱም ኪዳን ላይ ተገኝተው አያውቁምና ነው፡፡ ታዲያ እርሳቸው
ያለተገኙበት ኪዳን ላይ ግቢ ጉባዔው አልተገኘም ብሎ መጠየቅ ምን ይሉታል፡፡ ማለቴ እርሳቸው ግቢ ጉባዔው ኪዳን ስለማድረስ አለማድረሱ
በምን አወቁ ማለቴ ነው፡፡ በዚያ ላይስ ቢሆን ተማሪዎች ናቸውና ከረፈደባቸው ምን ማድረግ አለባቸው የግድ ኪዳን ማድረስ አለባችሁ
ሊላቸው የሚችለው ማን ነው፡፡ ጊዜ ያለው ያደርሳል ጊዜ የሌለው ደግሞ ወደ ትምህርቱ ይሄዳል በዋናነት ደብረ ማርቆስ የመጡት ለትምህርት
ነውና፡፡ እስኪ የቤተክህነት ሰዎች አስተምረው መክረው ጠዋት ለጸሎት የሚተጋ ምእመን ያፈሩ ከሆነ መረጃ አቅርቡልን የለማ ከገንዘብ
ውጭ ሌላ ታስባላችሁ እንዴ ያውም ቄስ ሙሉ አረ በፍጹም እየተዋወቅን፡፡
7.
ባለ ሦስት ደመወዙ መምህር ባሕረ ጥበብ የማኅበረ ቅዱሳን
የስራ ድርሻ ልጆችን ቤተ-ክርስቲያን በር ላይ ማድረስና በር ማሳየት ሲሆን ከድርሻው ከፍ ብሏል በማለት ተናግሯል፡፡ ይህ ሰው ሦስት
ደመወዝ የሚከፈለው ባለ ሦስት ቢላዋ ነው፡፡ ማኅበሩ የቤተክርስቲያንን በር ብቻ የማሳየት ሥራ ነው መሥራት ያለበት ብሏል፡፡ ከዚያ
በኋላስ ማስተማር የለበትም ወይ፡፡ ቤተክርስቲያን ውስጥ ሲገቡ የሚያገኙት ማንን ነው፡፡ አንተን እና መሰሎቻችሁን እኮ ነው፡፡ አባ
ማርቆስም አባ ማርቆስ ናቸው፣ ቄስ ሙሉም ያው ቄስ ሙሉ ናቸው፣ የቅባቱ አዝማሪ ዘላለም ተመስገንም ያው ዘላለም ነው፡፡ የተሐድሶ
መናፍቁ ንጉሥ አስራደም ያው ንጉሥ ነው ዘማዊው ዲያቆን በረከት ሞላም ያው በረከት ነው፡፡ አያችሁ እንግዲህ ቤተክርስቲያን ሲገቡ
ማንን እንደሚያገኙ፡፡ ታዲያ አደራ ተቀብሎ በሩን አሳይቶ ለጅብ ጥሎ ወዴት ይሄዳል ከጅቡ ጋራ ጉረሮ ለጉረሮ ተናንቆ በጎችን ይጠብቃል
እንጅ፡፡ እናንተ መልካም እረኛ መሆን ሲያቅታችሁ ምን ይደረግ እንግዲህ፡፡ አረ ማኅበሩን ያስፋው ያሳድገው ፈጣሪ፡፡
8.
መልአከ ፀሐይ አባ ወልደ ትንሳኤ ባንቲገኝ የቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ
ደግሞ ንግግራቸውን ሲጀምሩ ባዶ ቀሚስ ብቻ የለበስኩም አይደለሁም መርጌታም ጭምር ነኝ ብለዋል፡፡ ባዶ ቀሚስ ማለት ምን ማለት ነው
???ባዶ ቀሚስ ብቻ የለበስኩ አይደለሁም የሚለው ንግግር ሁለት ነገሮች ጎልተው ይታያሉ አንደኛ ለምንኩስና የወረደ/ዝቅ ያለ ክብር
መስጠትን ያሳያል ሁለተኛ ባዶ ቀሚስ ብቻ የለበስኩ አይደለሁም መርጌታ ጭምር ነኝ ማለት ከመካካላችን ካለነው መነኮሳት ውስጥ ያልተማረ
አለ ብሎ ለመናገር የተጠቀሙበት ንግግር መሆኑን መረዳት ቀላል ነው ፡፡ የሰ/ት/ቤት አባላት የመጡት ከወረዳ ነው ስለዚህ የአካባቢው ተወላጅ ልጆችን እያሰሯቸው አይደለም የሚል ሀሳብ
አንስተዋል በሀሳብ ብቻ አይደለም ከስብሰባው ቀን በፊት አሳፋሪ ደብዳቤም ጭምር ጽፈዋል እንጅ ፡፡ ይህንንም በተከታታይ አቅርቤላችኋለሁ፡፡
ስግደትን በተመለከተ ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል አዳራሽ ስገባ ሴቱም ወንዱም ተፋፍገው ላብ በላብ ሆነዋል ታዲያ የዘንድሮን ምከሩ ቀጣይ
ጀምሮ ግን መቆም አለበት የሚል ነገር ነግሬአቸውም ነበር የሚል ሀሳብ ሰጥተዋል ፡፡ ስግደትን ላብ በላብ ሆነዋል ብሎ መግለጽ አንድ
መርጌታ ነኝ ከሚል መነኩሴስ ይህ ቃል መውጣት አለበት ወይ፡፡ ላብ በላብ የሆኑት እኮ ሲሰግዱ ሲጸልዩ ነው እንጅ በሌላ ጉዳይ አይደለም፡፡
ላብ በላብ ሆኑ ብሎ ስግደትን ከማስቀረት ይልቅ ላብ በላብ የማያደርግ ሰፊ አዳራሽ መስጠት አይበጅም ነበር ወይ፡፡ ስግደት ግን
ላብ አያስመጣም ወይ አረ በጣም የሚገርሙ መነኩሴ ናቸው ቢያንስ ሌላው ይቅር ስንክሳር አንብበው አያውቁም ወይ፡፡
9.
አባ እንባቆም ጫኔ ሥራ አስኪያጁ ሌሎች አህጉረ ስብከቶች ጋር ማኅበረ ቅዱሳን እጅና
ጓንት ሆነው እንደሚሰሩ እናውቃለን የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው ፡፡ ሚናውን መለየት አለበት ከአገልጋይነት ወደ መሪነት
እየመጣ ነው ፡፡ ከኢትዮጵያ ፓትርያርክ ጋርም የገጠመ ነው ፡፡ ቅድስት ቤተ-ክርስቲያንን ሊታደግ የተቋቋመ ማኅበር ነው፡፡በተሠጠው
ደንብ ይመራ፡፡ የጥሉ ምክንያት ገንዘብ አይደለም ሃይማኖት ነው የሚል ሀሳብም ጨምረዋል፡፡ አባ እንባቆም አፍ ከፍቶ ፊትን ፀፍቶ
የሚያናግረው አምላካችን አናግሯቸው እንጅ አስበው የተናገሩት ንግግር ግን አይደለም ፡፡ እርግጥ ነው ጉዳዩ እርሳቸው ከመነኮሱበት
የቆጋ ኪዳነ ምህረት ገዳም አሳታሚነት የታተሙት መጻሕፍት መሆናቸው ለማንም ግልጥ ነው ታዲያ መፍትሔው ምንድን ነው ሊሉን ነው፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን እና ቤተክርስቲያናችን ቅባት ይኹኑ ነው ወይስ እናንተ ተዋሕዶ ልትሆኑ ነው መፍትሔው ቢገለጽ ጥሩ ነበር፡፡
10. የዘንድሮው ጥል መሰረቱ
የገንዘብ አይደለም ሃይማኖት ነው (አባ እንባቆም ጫኔ) ብለዋል፡፡ ያ ከሆነ ጥሩ ራሳችሁን ፈትሹ፡፡
በቤተክህነቱ በኩል
የተሰጡ መልሶች ምን ነበሩ የሚለውን እና ሌሎችንም ጨምሬ እመለስበታለሁ፡፡
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ