ሐሙስ 12 ኦክቶበር 2017

አባ እንባቆም ጫኔ VS ምሥራቅ ጎጃም




ዛሬ ጥቅምት 2/2010 ዓ.ም ነው፡፡
==========================
• ጸሎቱ እንደተጠበቀ ነው፡፡ የጥቅምቱ ሲኖዶስ አንድ መላ እንዲሰጠን ወደ ፈጣሪ እየተማጸንን ነው፡፡
• እነርሱ ለጥፋት 24 ሰዓት እየሠሩ ናቸው እኛ ለድኅነት እንቅልፍ ሊያሸንፈን አይገባውም፡፡
• ብቸኛው ምርጫ ወደ ፈጣሪ መጸለይ እውነት እውነቱን መነጋገር ብቻ ነው፡፡
• ይህ ፖስት ውሸት ነው የምትሉ ሰዎች በመረጃ አስደግፋችሁ ውሸት መሆኑን አሳውቁ ከዚያ ውጭ ዝም ብየ እለፈልፋለሁ ብትሉ እብድ ያሰኛችኋል፡፡

ሊቀ ማእምራን አባ እንባቆም ጫኔ ይባላሉ የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ስራአስኪጅ ናቸው፡፡ በጥንቆላ እና በመተት ሥራቸው አገር ያውቃቸዋል ግን ለአባ ማርቆስ የቀኝ እጅ ናቸው፡፡ አባ እንባቆም ጫኔ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተምረውም ዲግሪያቸውን ያገኙ ናቸው፡፡ ከሁለት ጊዜ በላይ የሀገረ ስብከቱን መኪና ሲያሽከረክሩ ከመኪና ጋር እየተጋጩ ከሞት አፋፍ የተረፉም ተአምር የተደረገላቸው ሰው ናቸው፡፡ ምንኩስናቸው የተፈጸመው ሁለቱ የቅባት መጻሕፍት የታተሙበት ምስካበ ቅዱሳን ቆጋ ኪዳነ ምሕረት ገዳም እንደሆነ የውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ ፡፡ ይህ ሁሉ የግል ታሪካቸው ምንም ባይፈይድልንም እንደመግቢነት እንድትጠቀሙበት ጽፈነዋል፡፡
አባ እንባቆም ጫኔ እንደ አንድ ግለሰብ ለዚህ ህንጻ እዚህ ደረጃ መድረስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ እንደሆኑ ማንም ይመሰክራል፡፡ እውነቱን እውነት ማለት ተገቢ ስለሆነ ነው፡፡ አባ ማርቆስ ሲያሞግሷቸው “መቼ ይበላሉ መቼ ይጠጣሉ መቼ ይተኛሉ እያልኩ እገረማለሁ” ብለዋቸዋል ትክክል ናቸው፡፡ ለዚህ ህንጻ ብዙ ለፍተዋል ብዙ ደክመዋል እንደ ግለሰብ ሆኖም ግን ባለው አጠቃላይ ሃይማኖታዊ ጉዳይ ላይ ችግር አለባቸው ያውም መሠረታዊ ነዋ፡፡ ቄስ አበበ ያን ያህል ለፍተው ያን ያህል ደክመው መናፍቃንን ሲሸልሙ ቄስ አበበን ግን ስማቸውም እንዳይነሣ ነው የተደረገው ለምን እንደሆነ እነርሱ ብቻ ናቸው የሚውቁት፡፡
ወደ ሪፖርታቸው እንሂድ በነገራችን ላይ የሪፖርቱን ሙሉ ቃል ከዚህ ጋር የተያያዘውን ቪዲዮ ተመልከቱት፡፡ እኔ ግን ውሸት የሆኑትን ያልተደረጉትን እንደተደረጉ አድርገው ያቀረቡትን ሁሉ እየነቀስሁ እነግራችኋለሁ፡፡ እናንተ ሙሉውን አድምጡት በነገራችን ላይ ከጥቂት ጉዳዮች በስተቀር የአባ እንባቆም ሪፖርት ውሸት እንደሆነ ትገነዘባላችሁ ብየ አምናለሁ፡፡ አባ ማርቆስ በዚህ ሀገረ ስብከት እንዲቀጥሉ ለማድረግ ብቻ ታስቦ የተደረሰ የፈጠራ ሪፖርት ነው ይህንንም እናንተ ጭምር እንድትታዘቡ ይኸው እነግራችኋለሁ፡፡
https://www.facebook.com/metshetewahido/videos/pcb.1931858523698408/1931857163698544/?type=3&theater

1. ‹‹ሀገረ ስብከቱ በርካታ ቅርሶች ያሉት በርካታ ጥንታውያን አድባራት እና ገዳማት ያሉት በተፈጥሮ ሃብት የታደለ ሊቃውንት የሚገኙበት እንደሆነ ገልጸው ይህ ሁሉ ሃብት እና ንብረት ያለውን ሀገረ ስብከት የሚያለማው ጠፍቶ የነበረሲሆን አሁን ግን የልማት እና የወንጌል አባት የሆኑት አባ ማርቆስ ሀገረ ስብከቱን ከተረከቡበት ከ2004 ዓ.ም ጀምረው ግን እንዳለሙት ወንጌል እንዳስፋፉበት ገለጹ›› ይህ ፖሊቲካዊ አጀንዳ ያነገበ ሪፖርት ነው፡፡ አሁን ያለው መንግሥት ድሮ በአጼዎች እና በደርግ ዘመን ይች አገር ምንም ያልነበራት ነበረች አሁን እኛ ከያዝናት ጀምሮ ግን ለምታለች አድጋለች እያለ እንደሚናገረው ያለ ማለት ነው፡፡ በእውነት ግን አብማ ማርያምን ያህል ከኢትዮጵያ አንደኛ ሊባል የሚችል ህንጻ ያስገነቡ አባ ማርቆስ ናቸውን? አይደሉም፡፡ ዋሻው ቅዱስ ሚካኤል ህንጻ መቼ ነው የተሠራ? ደጀን አበ ብዙኃን አብርሃም የሚባለው አክሱም ጽዮንን የመሰለው ህንጻ መቼ ነው የታነጸው? ሞጣ ወረዳ የገብርኤል ቤተክርቲያን በሚያምር መልኩ የተገነባው መቼ ነው? ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ አለ ያገሬ ሰው፡፡ በልማቱስ በወንጌሉስ በረከታቸው ይድረሰንና አቡነ ጴጥሮስን የሚተካከላቸው አልነበረም ዳሩ ግን ዐረፍተ ዘመን ገታቸው እንጅ፡፡ ታዲያ ምስራቅ ጎጃም ላይ ከአባ ማርቆስ ውጭ ሥራ የሠራ የለም ብሎ መናገር ምን የሚሉት ድንቁርና ነው፡፡ አሁን ማን ይሙት አቡነ ማርቆስ በምን መስፈርት ነው የልማት እና የወንጌል አባት ሊባሉ የሚችሉት በምን መመዘኛ እኮ በምን!!! እኮ ስል ደግሞ አባ ማርቆስን መሰልኳችሁ አይደል እኮ መሰልኳችሁ አይይይ ክክክክክ፡፡ አረ አልመስልም!!! አባ ማርቆስ ማለት እኮ ገዳማትን የመዘበሩ ቅርሶችን የዘረፉ ናቸው፡፡ ለዚህ በርካታ ማሳያዎችን ማቅረብ እንችላለን፡፡ ለገንዘብ ዘረፋው በይፋ የወጣውን የገዳመ አስቄጥስ ተክለ ሃይማኖትን ገዳም ጠይቁ፡፡ የባህረ ጥምቀቱን ህንጻ አሠሪ ኮሚቴ አነጋግሩ፡፡ የሀገረ ስብከቱን ህንጻ ያሠሩ ኮሚቴዎችን ጠይቁ፡፡ ለቅርስ ዘረፋው ደግሞ ዲማ ጊዮርጊስን መርጡለ ማርያምን ጎብኙ፡፡ መርጡለ ማርያም ላይ በቅርሶች ጉዳይ ከፍተኛ ውጥረት ላይ ናቸው፡፡ መምህር ምትኩ ደምሌ የሚባሉ ቦታውን ከልጅነታቸው ጀምረው የሚውቁት መዘምር እስካሁን ድረስ እየተከራከሩ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ዲማ ላይ ደግሞ አባ ማርቆስ በመደቧቸው አባ ፍቅረ ሥላሴ በሚባሉ በእነማይ ወረዳ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ በኩል ብዙ ትግሎችን አድርገዋል፡፡ ሆኖም ግን በዲማ ጠንካራ ማኅበረሰብ ትብብር ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡ ይህንንም ባለፈው ዓመት “የዲማው ጦርነት” በሚል ርእስ መረጃውን ሰጥቻችሁ ስለነበር ታስታውሳላችሁ ብየ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ሌላው አባ ማርቆስ የወንጌል አባት የሚባሉት ሴት ልጅ ስትደርስ ታስታውቃለች እያሉ በድንች እየመሰሉ ስላስተማሩ ነውን? ሰኔ ጎልጎታ ልብ ወለድ ነው ስላሉ ነውን? ተዝካር ምዋርት ነው ስላሉ ነውን? ተአምረ ማርያም አያስፈልግም ስላሉ ነውን? በልተው ልቀድስ ስላሉ ነውን? የዐቢይ ጾም ከበሮ ካልተመታ ካልተጨበጨበ አይደምቅም ስላሉ ነውን? ገና በ28 በ29 ተከበረ ለምን ትላላችሁ ይህ እኮ ካሌንደር ነው ስላሉ ነውን? ቅባት ተዋሕዶ ጸጋ ካራ አትበሉ ቃል ሃይማት አይሆንም ስላሉ ነውን? ወልድ ዋሕድ በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ ስላሉ ነውን? ሰንበት ትምህርት ቤቶችን ስለዘጉ ነውን? የማኅበረ ቅዱሳንን ቢሮዎች ስለቆለፉ ነውን? ስግደት እና ምሕላ አያስፈልግም ስላሉ ነውን? ወዳጄ ወንጌልን እና ወንጀልንማ እንለይ እንጅ፡፡ የወንጀል አባት ካላችሁ እንስማማለን፡፡ እስኪ የት ገጠር በእግራቸው ሂደው ነው ወንጌልን ያስፋፉት የትኛውን ኢአማኒ አጥምቀው መልሰው ነው የወንጌል አባት የተባሉት፡፡ መድረክ ላይ ቆመው ዋዛ ፈዛዛ እየተናገሩ ከማሳቅ በቀር ጥቅስ ጠቅሰው ያስተምራሉ ወይ፡፡ በዚህ እጅ እጅ በሚለው የቤተክርስቲያኒቱ ቴሌቪዥን ጣቢያ ብዙ ጊዜ ታይተዋል እኮ ከትራፊክ አደጋ ውጭ ይናገራሉ ወይ ? አረ ሰው ያፍርባችኋል
2. ሀገረ ስብከቱ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት የሚልከው 35% የሰበካ ጉባዔ ገቢ አባ ማርቆስ ከመምጣታቸው በፊት 40ሺ የነበረውን አሁን ግን ከ80% በላይ እጥፍ በማድረግ 3 ሚሊዮን 2 መቶ ሺህ ብር ገቢ እያደረግን ነው ብለዋል ክቡር ሥራ አስኪጁ፡፡ የዚህን እውነታ ጠቅላይ ቤተክህነት የሚሠሩ ሰዎች ይወቁት እውነት ቢሆን እንኳ እዚህ ላይ የአባ ማርቆስ ድርሻ ምንድን ነው? ከደመወዛቸው ቀንሰው ያበረከቱት ገንዘብ እኮ ነው ያስመሰሉት፡፡ ይህ ብር እኮ ከድኃው አማኝ የተሰበሰበ ገንዘብ ነው፡፡ አባ ማርቆስ መጡም አልመጡም አማኙ ገንዘብ መክፈሉ አይቀርም፡፡ በወንጌል አሳምነው ኢአማንያንን አጥምቀው አዲስ የሰበካ ጉባዔ ክፍያ ከፋዮችን ወደ ቤተክርስቲያኒቱ አስገብተው ቢሆን ኖሮ ይወደሱ ይሸለሙም ነበር፡፡ ግን ያሳመኑት ሰው በሌለበት ሁኔታ ከአባ ማርቆስ በፊት 40 ሺህ የነበረው ዛሬ 3ሚሊዮን የሚገባበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለም፡፡ ትዝብቱን ለራሳችሁ ተውሁት!
3. ካርታ እና ፕላንን በተመለከተ ያነሡት ጉዳይን ስንመለከት “ሀገረ ስብከቱ ለቢሮነት የሚጠቀመውን 3000 ካሬ ሜትር ቦታ ካርታ እና ፕላን አሠርተናል፡፡ የከተማው አድባራት እና ገዳማት የሚጠቀሙበትን ባሕረ ጥምቀት የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር አሠርተን ወደ ማልማቱ ገብተናል” ይላሉ፡፡ አቡነ ማርቆስ ይህንን ካርታ እና ፕላን ለማሠራት የሠሩት ሥራ ምንድን ነው? እውነቱን ስንነጋገር ለዚህ ካርታ እና ፕላን ከፍተኛ ሥራ ሲሰሩ የነበሩት ብጹእ አቡነ ጴጥሮስ ናቸው፡፡ የዚህ ሃሳብ ጠንሳሽ እና እስከ መጨረሻው ድረስ ሲከታተል እና ሲታገል የነበረውም ማኅበረ ቅዱሳን ነው፡፡ እያንዳንዱ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ካርታ እና ፕላን የተሠራለት አቡነ ማርቆስ ምሥራቅ ጎጃምን ገና ሳይረግጡ ነበር፡፡ ይችን ሁለት ነገር ሠሩ ተብሎ የድሮ አባቶቻችንን ሥራ መደፍጠጥ ምን ይሉታል ለዚያውም እርሳቸው ባልሠሩት ነገር ላይ፡፡ እርሳቸውማ የጥምቀት ባህሩንም መንግሥት ለልማት እፈልገዋለሁና ገንዘብ ሰጥቼዎት ይልቀቁልን እንደተባሉና እንደተስማሙ እየተነገረባቸው እኮ ነው፡፡ እያለማን ነው የምትሉትስ ኮሚቴውን ማፍረሳችሁን እንደ ማልማት ቆጥራችሁት ነው እንዴ? በነገራችን ላይ አባ ማርቆስ ይህን የተመረቀውን ህንጻ አስይዘው ከንግድ ባንክ ሊበደሩ ሲሉ በባንኩ ብርቱ ጥረት ሊከሽፍባቸው እንደቻለ ረሰታችሁት ነው ይህንን የምትነግሩን፡፡
4. የአገልጋዮችን ደመወዝ በተመለከተ ደግሞ አስቂኝ ነገር ተናግረዋል፡፡ አቡነ ማርቆስ ሀገረ ስብከቱን ሳይረከቡ ዲያቆን 70 ብር ካህን 150 ብር መምህራን 200 ብር አስተዳዳሪዎች 300 ብር የነበረውን ደመወዛቸውን በማሻሻል ዛሬ አቡነ ማርቆስ ከመጡ በኋላ ዲያቆን 2700 ብር ካህን 3000 ብር መምህራን ከ3500 ብር በላይ አስተዳዳሪዎች ደግሞ ከ4000 ብር በላይ እየተከፈላቸው ነው ብለዋል፡፡ ይህ ጉዳይ በእጅጉ ያስተዛዝበናል፡፡ በእውነት የሚቀድሱበት ልበስ አጥተው እጣን እና ጧፍ አልቆባቸው ዲያቆናት እና ካህናት ጠፍተው ተሰደው የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናት ባለበት ሀገረ ስብከት ላይ ይህን ያህል ደመወዝ እየከፈልን ነው ሲሉ አለማፈራቸው፡፡ ይህ ደመወዝ የዓመት ደመወዝ ነው እንጅ የወር ደመወዝ አይደለም፡፡ ለተወሰኑት ግን ምናልባትም የአቡኑ ዘመዶች ለሆኑ VIP ዲያቆናት ካህናት መምህራን እና አስተዳዳሪዎች ሊከፈል አይችልም ብለን አንሟገትም፡፡ ለዘመዶቻቸውማ ከዚህም በላይ ይከፍላሉ ሀገረ ስብከቱ ማለት ግን የአባ ማርቆስ ዘመድ አዝማዶች ብቻ ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ እኔ ያነጋገርሁት አንድ ዲያቆን ዘመድ ያልሆነ ማለቴ ነው ደመወዙ በዓመት 1500 እንደማይደርስ ነው የነገረኝ፡፡ እንዲያውም እህል ብቻ እየተሠፈረላቸው የሚያስተምሩ መምህራንም እንዳሉ ነው ያወራኝ፡፡ ታዲያ ዲያቆን ካህን መምህር አስተዳዳሪ የሚባለው የከተማው ብቻ የአቡኑ ዘመዶች ብቻ ናቸው እንዴ እስኪ ወደ ወረዳ ወጣ በሉና ለማነጋገር ሞክሩ፡፡ይህን ውሸት ሪፖርት ላይ ያካተቱት አቡነ ማርቆስ ከመጡ ወዲህ ሀገረ ስብከቱ ተለውጧል አድጓል ለማለት ነው፡፡
5. ሕንጻውን ለመገንባት በጠቅላላው 19 ሚሊዮን 49 ሽህ 556 ከ08 ከ ሳንቲም ነው ብለዋል፡፡ በነገራችን ላይ እዚህ ላይ በስጦታ በድጋፍ በጉልበት ወዘተ የወጣውን ሙሉ ወጭ ዝርዝር መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ እናንተው ተከታተሉትና ይህን የምትመለከቱትን ህንጻ ለማነጽ ይህ ገንዘብ በቂ ነውን ወይስ በዝቷል የሚለውን ራሳችሁ ፍረዱ፡፡ ይህ ህንጻ ዘመናዊ ትምህርት ቤት እና ሁለገብ ህንጻ ተብሎ ቢገነባም እስካሁን ድረስ ግን ትምህርት ቤቱም አልታየም፡፡ እንዲያውም ለግል ኮሌጆች ተከራይቶ ነው የሚገኘው፡፡
6. የአገር ፍቅር ያላቸው አቡነ ማርቆስ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ እስከ ውጭ አገር ድረስ ለክብራቸው ሳይጨነቁ ይህን ህንጻ ለዚህ ደረጃ በማብቃትዎ እንኳን ደስ አለዎ ብለዋቸዋል፡፡ እንዲያውም ሽልመትም አዘጋጅተው ሸልመዋቸዋል፡፡ አስቡ ራሳቸው ለራሳቸው ሽልማት አይ አንቺ የቅጥፈት ጊዜ ምን ይውጥሽ ይሆን፡፡ ህንጻውን አስይዘው ሊበደሩ ሲሉ እንደከሸፈባቸው እንጅ ህንጻውን ለማስገንባት እንደደከሙ አናውቅም ነበር፡፡ በየወረዳው ግን ለልመና ሲወጡ ቅባትን እያስተማሩ ይመጡ እንደነበር እናውቃለን፡፡ ህንጻውን ለዚህ ደረጃ ያበቁትማ ስማቸው እኮ አልተጠራም፡፡ እነ ቄስ አበበ አልተጠሩም፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን አልተጠራም፡፡ ግቢ ጉባዐየ አልተጠራም ሰንበት ትምህርት ቤት አልተጠራም፡፡ ይህ ሁሉ ስንት ሥራ እንደሠራ እያወቅን አስሬ አቡነ አቡነ ማለት ምንድን ነው፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን አባል የሆነው ኢንጅነር ኤልያስ ከመሠረት ጀምሮ እስከ ፍጻሜው ድረስ ዲዛይን ከማውጣት እስከ ግንባታ ክትትል ድረስ በነጻ እንደሠራው ይታወቃል፡፡ ይህ ኢንጅነር ሳይሸለም ማን ይሸለማል የተሐድሶው መናፍቅ ይኸነው ነዋ፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ከ2 መቶ ሺህ ብር በላይ ከዋናው ማዕከል እንዲሁም ከደብረ ማርቆስ ማእከል ወደ 7 መቶ ሺህ ብር ተበርክቷል፡፡ ከውጥኑ ጀምሮ እስከፍጻሜው ድረስ ደፋ ቀና ሲል የነበረው ማኅበረ ቅዱሳን እንኳን እውቅና ሊሰጠው አቡነ ማርቆስ ሊዘጉት ሲያሳድዱት ማየት በጣም ይደንቃል፡፡ ባጎረስኩ እጄን ተነከስኩ ማለት ይኼ ነው፡፡ የህንጻው ዲዛይን እና የግንባታው ክትትል ብቻ ወደ ገንዘብ ቢቀየር ምን ያህል ገንዘብ ይሆናል እርሱን ግንባታ ላይ ላላችሁ ወገኖች አሳይመንት ይሁናችሁ፡፡ እንድማጣ ላይ እያንገላቷቸው ያሉት የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ጉባዔ ግምቱ 5 መቶ ሺህ ብር የሚደርስ የጉልበት ድጋፍ አድርገዋል ግን ስም አጠራራቸው የለም ለምን ሲባል አባ ማርቆስ ማኅበሩን ስለሚሉት ብቻ ነው ሌላ ምን ምሥጢር አለው ብላችሁ ነው ለምን ጠሉት ግን ብላችሁ አንድ ቀን የሚያሳድር ነገር እንዳትጠይቁኝ፡፡ ሌላው አሁን አባ ማትያስ የመሠረት ድንጋይ ያኖሩበት የፈለገ አርዝ ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ የተቀረጸው በደብረ ማርቆስ ማዕከል የማኅበር አባል በሆኑ ልጆች ነው፡፡ አባ ማርቆስ ስማቸውን እየጠሩ ሲሰድቧቸው የሚውሉት እነዚህ ልጆች ይህን ፕሮጀክት ቀርጸው አበርክተዋል፡፡ ግን ማን ስማቸውን ጠርቶ እውቅና ይስጣቸው፡፡
7. የደብረ ማርቆስ ከተማ 98% ኦርቶዶክስ ነው ያሏት ሪፖርት እንዴት እንዳስገረመችኝ አትጠይቁኝ፡፡ ይችን የተናገሯት መጀመሪያ አካባቢ ነው፡፡ ይህንን የቀረጸው ልጅ ራሱ ገርሞት “ኦርቶዶክስ” ብሎ አብሮ ተቀርጾአል፡፡ “ተዋሕዶ” ብላችሁ እንዳትናገሩ አፋችሁን የለጎመው ማን ነው፡፡ ወደዱም ጠሉም ሥራ አስኪጅነትዎ “በኢትዮጵያ ኦርቶዶስ” ሳይሆን “በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ” ሥር ነው፡፡ አሁን 98% ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ነው ቢሉ ምን አለበት፡፡ ለነገሩ “ተዋሕዶ” ን አባ ማርቆስም አያውቁትም አይወዱትም እርስዎስ የአባው ልጅ አይደሉ፡፡ እንዲያውም እኮ ለአባ ማትያስ እንዴት ያለ ልጅ መሰልዎ ነገ የቅዱስነትዎ ልጅ ሊሆን የሚሆን ነው ተብለው ነገ ጵጵስናው ላይም እንደምናይዎ ተስፋ ተጥሎብዎታል፡፡
ሽልማቶችን በተመለከተም አሳፋሪ ነገር ዓይተናል፡፡ ቆዩ ይኼነው የተባለው ተሐድሶ የተሸለመ በምን ምክንያ ነው? ከ17ቱ ወረዳ ቤተክህነቶች ሁሉ ተለይቶ የቅባት መጻሕፍትን በነጻነት የሚሸጠው ወረዳ ቤተክህነት ጉንደ ወይን አቡነ ማርቆስን እንዲሸልም ምን አነሣሣው? የሀገረ ስከቱ ሥራ አስኪጅስ የሀገረ ስብከቱን ሊቀ ጳጳስ መሸለም ምን ማለት ነው ራስ ለራስ ይሸልማል እንዴ ታይቶ የማያውቅ አዲስ ነገር አመጡብን እኮ፡፡
በዚህም ይበል በዚህ ይህ ሁሉ መርኃ ግብር ሲደረግ የማርቆስ ህዝብ ጨዋነቱን አስመስክሯልና ይደነቃል፡፡ በፓትርያርኩ ፊት አጉል ንትርክ ማንሣት አልፈለገም ነበር፡፡ መንግሥትም ችግሩን እኔ እፈታለሁ ብሎ ስለነበረ ችግሩን መንግሥት እንዲፈታው ህዝቡ ይማጸናል፡፡ በአቡነ ማርቆስ በኩል ያለው ችግር ግን ዳር ሳይደርስ አርፎ የሚተኛ ሰው የለም፡፡ አሁንም ወደፊትም እንታገላቸዋለን፡፡ ትግላችን ደግሞ ከዚህ ሀገረ ስብከት እንዲነሡ ብቻም አይደለም ስለክህደታቸውም ምላሽ እንዲሰጡበት ጭምር እንጅ፡፡
ቀጣይ ላይ የአቡነ ማርቆስን ንግግር ጠብቁ፡፡
#የቅዱስ_ማርቆስ_ሰንበት_ትምህርት_ቤት_ላይ_የተጣለውን_ከባድ_አደጋም_በቅርቡ_አደርሳችኋለሁ፡፡
ዘመነ ማርቆስን ለቤተክርስቲያናችን እናድርገው፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

አባ ወልደ ትንሣኤ ባንቲገኝ VS መልእልተ አድባር ቅዱስ ማርቆስ ሰ/ት/ቤት

ዛሬ ጥቅምት 5/2010 ኣ.ም ነው፡፡ ============================= ·          ጸለተ ምሕላው እንደቀጠለ ነው፡፡ ·          ጽጌን በቤተክርስቲያን እያደርን በረከተ ሥጋ ወነ...